army

SelamAbesha.com

ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ በርካታ ግዳጆችን የሚፈፅም መከላከያ ሰራዊት ገንብታለች - አቶ ሲራጅ ፈጌሳ

May 25,2016

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 25 አመታት በተከናወኑ ስራዎች በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጆችን መፈፀም የሚችል የመከላከያ ሰራዊት መገንባት ተችሏል አሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ።

 

ሚኒስትሩ የተለያዩ የውጭ እና የውስጥ ፀረ ሰላም ሃይሎች በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ቢያደርጉም በሰራዊቱ ብርቱ ስራ ሀገሪቱ ሰላሟ ሳይናጋ በልማት ጎዳና ቀጥላለች ነው ያሉት።

 

ከተለያዩ የመከላከያ ሰራዊት ክፍሎች የተውጣጡ አባላት በአዲስ አበባ የፓናል ውይይት እያካሄዱ ነው።

 

ሀገሪቱ ከ25 አመት በፊት ከነበረችበት ግጭት ወጥታ አሁን እያስመዘገበችው ላለው ሁለንተናዊ እድገት መከላከያ ሰራዊቱ ያስመዘገበው ውጤት በውይይቱ በስፋት ተነስቷል።

 

በዚህም ሰራዊቱ የሻዕቢያ መንግስትን ጨምሮ የሀገሪቱ ሰላም እና እድገት ከማይዋጥላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚቃጡ ትንኮሳዎችን በማክሸፍ ህዝቦች ሰላማዊ አየር እየተነፈሱ የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ ወጤታማ ተግባራትን ማከናወኑ ተጠቁሟል።

 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተውጣጣ መሆኑም ተነስቷል።

 

ሰራዊቱ የሀገሪቱን ሰላምና ደንበር ከማስከበሩም ባለፈ በጎረቤት ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች አኩሪ ገድል እየፈፀመ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ሀገሪቱ ከ12 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪዎችን ማሰማራቷን አብራርተዋል።

 

ይህ ውጤት በሶማሊያ የተሰማራውን የአሚሶም ሰላም አስከባሪ ሀይል የተቀላቀለውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አይጨምርም፤ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ያሰማራች የአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ናት ብለዋል አቶ ሲራጅ።

 

መከላከያ ሰራዊቱ የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት።

 

በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው፥ ሰላም እና ልማትን የሚያደናቅፉ ሀይሎችን ለመጠበቅ እና በሀገሪቱ እድገት የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት እንደሚተጉ ተናግረዋል።

 

በተያያዘ የውጭ ጉዳይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት፣ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት እና የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞችም የግንቦት 20ን 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓልን አክብረዋል።

 

በ25 ዓመታት ጉዞው የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በውይይት መድረኮቹ ተፈትሸዋል።

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED