Africa_day

SelamAbesha.com

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንን በየዓመቱ ማክበር የሚያስችላት ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ነው

May 25,2016

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2008 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንን እንደ ሌሎች ብሔራዊ በዓላት ማክበር የሚያስችላት ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

 

የቀድሞ አፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ምስረታን ለማስታወስ 'የአፍሪካ ቀን' ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በፓናል ውይይት ዛሬ ተከብሯል።

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት ነፃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ መጠን ቀኑን በየዓመቱ ለማስታወስ እየተዘጋጀች ነው።

 

ዕለቱ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካኒዝም ጥላ ሥር ተሰባስበው ቅኝ ገዢዎችና ጨቋኞችን ከአህጉሪቱ ለማስወገድ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማስታወስ ይከበራል።

 

በየዓመቱ ግንቦት 17 ለአሕጉሪቷ ነፃነት ሰማዕት ለሆኑ ጀግኖች አፍሪካውያን የሚገባቸውን ክብር ሊሰጡ ይገባል፤ ዕለቱም ይህን የሚወክል ይሆናል ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ ከቀደሙት ዘመናት ጀምራ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉት በጋራ ሆነው ሲታገሉ ነው የሚል ጽኑ አቋም ስታራምድ መቆየቷን አምባሳደር ታዬ አውስተዋል።

 

በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አማካኝነት በተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተሸጋገረ በኋላም ይህን አቋሟን ተግባራዊ በማድረግ የላቀ ሚና እየተጫወተች መሆኗን ገልጸዋል።

 

ከዚህ አኳያ ቀኑ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓላት እንዲከበር ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን አስታውቀዋል።

 

የአፍሪካ ቀን ሲከበር የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ እንዲወለበለብ ይደረጋል።

 

"ኢትዮጵያ የኅብረቱ መቀመጫ አገር በመሆኗ ቀኑ ቢከበር የተሻለ ቦታ እንድታገኝ ያደርጋታል" ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዋህድ በላይ ናቸው።

 

ኢትዮጵያ ለኅብረቱ የእስካሁኑ ጉዞ ትልቅ ሚና ስትጫወት የቆየችና አሁንም አህጉሪቷን በምጣኔ ኃብት ትብብር ጉዳዮች፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎችና በሠላም ማስጠበቅ ረገድ የጎላ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

 

በተጨማሪም በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በመሪዎቿና በዲፕሎማቶቿ አማካኝነት የሚያኮራ ተግባራት ማከናወኗን አምባሳደር ዋህድ አስረድተዋል።

 

በውይይቱ ላይ 'የፓን አፍሪካኒዝም መልካም ውጤቶች' በሚል ርዕስ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አብዱል መሐመድ በወቅቱ አንድ ዓላማ ያነገበች አህጉር ለመገንባት ብዙዎቹ ዋጋ ከፍለዋል ነው ያሉት።

 

''ፓን አፍሪካኒዝም የሕዝቦች እንቅስቃሴ ነበር'' የሚሉት አቶ አብዱል ሂደቱ "በተወሰነ መልኩም ቢሆን የተሻለች አፍሪካን መገንባት የሚያስችል መሰረት ጥሎ ያለፈ ነበር" ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት ከመሆን ባለፈ አገራትን በማስተባበር ስለመብታቸውና ስለጥቅማቸው እንዲታገሉ የማነሳሳት ሥራ መስራቷን ገልጸዋል።

 

በውይይቱ ላይ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ቀኑ አፍሪካውያን አንድነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበትና ነፃነታቸውን የሚዘክሩበት የተለየ ዕለት ነው።

 

በአንፃሩ አፍሪካውያንን አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ የጋራ ፕሮጀክቶች የመተግበር፣ የማስፋትና የማጠናከር ሥራ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ የአህጉሪቷ ቀጣይ ፈተና ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED