‹‹ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነት እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ››

SelamAbesha.com

‹‹ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነት እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ››

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

31 Aug, 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታወቁ፡፡

 

 

በአሁኑ ወቅት በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተነሱ ጥያቄዎች ያልተገቡ ሕገወጥ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እንደሆነና እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ ለሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

 

በትግራይና በአማራ ክልሎች የወሰንና የማንነት ጥያቄና እስካሁንም ችግሩ ላለመፈታቱ የየክልሉ አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ‹‹ኢሕአዴግ ብቃቱ የሚለካው ችግሮች ሲያጋጥሙት ብቻ አይደለም፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙት በሚያካሂደው ሳይንሳዊ ትንታኔ ተመሥርቶ በሚወስደው ዕርምጃ ነው፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

 

‹‹በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ብቃቱ አልተሟጠጠም፤›› ብለው፣ ‹‹እዚህም እዚያም በተነሱ ግጭቶች አገሪቱ ትፈርሳለች የሚለው ሥጋት መሠረተ ቢስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ትገኛለች፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

 

ኢሕአዴግ ብቻ ይህ ችግር እንዳልገጠመው፣ ይልቁኑም ሌሎች ልማታዊ መንግሥታት ይህ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

 

‹‹ቱርክ ፈጣን ልማት ያመጣ መንግሥት ነው፡፡ አሁን ግን ችግር ገጥሞታል፡፡ ብራዚልና ኮሪያም ባካሄዱት ልማት ከችግር ወጥተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ ብራዚል ችግር አጋጥሟታል፤›› ብለዋል፡፡

 

‹‹ኢሕአዴግ ከዓመታት በፊት ልማቱን ሲጀምር 40 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከድህነት ወለል በታች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አሁን ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሕዝቦች ቁጥራቸው በግማሽ ቀንሶ ወደ 20 ሚሊዮን ወርዷል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከታዳጊ ኢኮኖሚ ወዳደገ ኢኮኖሚ እስኪደርስ ድረስ ችግር ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል፡፡

 

ነገር ግን ኢሕአዴግ ለተፈጠሩ ችግሮች ግምገማ ካካሄደ በኋላ ለችግሩ መባባስ የራሱ አመራሮችም እጅ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ዕርምጃም እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የራሷ የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም የውጭ ኃይሎች፣ በተለይ በውጭ ለሚኖሩ ጽንፈኛ ዳያስፖራ አባላት ከፍተኛ ገንዘብ መስጠታቸው በመረጃ መረጋገጡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን አልገለጹም፡፡

 

እነዚህ ዳያስፖራዎችም አብዛኛው ለራሳቸው ካስቀሩ በኋላ ከፊሉን ወደዚህ በመላክ ብጥብጥ እየፈጠሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይለ ማርያም ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሳው ችግር ላይ ምንም ባይሉም፣ ከሕዝብ ጋር በተሠራው ሥራ ግን መረጋጋት መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED