ፓርቲዎች ለመወያየት ተገናኝተው ሳይስማሙ ተለያዩ

SelamAbesha.com

ምክርቤቶቹ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ወሰኑ

Mon, Apr 30, 2018

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት 1ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለአንድ አመት እንዲራዘም ዛሬ ወሰኑ፡፡

 

የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ቆጠራው እንዲራዘም በስምምነት ላይ በመድረሱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት አስተላልፏል፡፡

 

በዚሁ በ5ኛው የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባቸው 4ኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማራዘም በቀረበው አጀንዳ ላይ የጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን አስፈላጊውን ዝግጅት ያደረገ ቢሆንም ከቆጠራው የሚገኘው መረጃ አስተማማኝና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ቆጠራው የሚካሄድበት ጊዜና ወቅት አመቺ ሊሆን ይገባል ተብሏል፡፡

 

የምክርቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ከሚል በዚሁ ጊዜ በአንዳንድ የሀገሪቱ ቦታዎች በተከሰቱ ችግሮች የሰዎች ከመደበኛ መኖሪያቸው መፈናቀል፣ የጸጥታ መደፍረስና ተዛማች ችግሮች ምክንያት ቆጠራውን ለማካሄድ የሚጠይቀውን አለም አቀፍ መስፈርትና የቅድመ ዝግጅቶች አጠናቆ ከመፈጸም አንጻር በአሁኑ ጊዜ ቆጠራውን ለማካሄድ የሚያስችል እንዳልሆነ ነው ያስታወቁት፡፡

 

በመጨረሻም 2ቱም ምክር ቤቶች ከተወያዩ በኋላ 4ኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አፅድቀዋል፡፡

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ ልዩ ስብሰባው 4ኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በ3 ተቃውሞና በ1 ድምፀ ተአቅቦ እንዲሁም የ20ኛ እና 21ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ ትናንት ማፅደቁ ይታወቃል ፡፡

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED