የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አራዘመ

SelamAbesha.com

በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ወደ ቀደሞ ስፍራው ተመልሷል- ጠ/ሚ ኃይለማርያም

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 08፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ወደ ቀደሞ ስፍራው መመለሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፥ የሀገሪቱ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ የዲፕሎማቲክ ማህብረሰቡ ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳ መነሳቱን አስታውሰዋል።

በቅርቡ በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው ሁከትም በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ፍሰትና ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው ጫና የከፋ አለመሆኑን ነው ያስረዱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላቱ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እነዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰላም እና መረጋጋት ላይ የመጣውን ለውጥ፤ መንግስት እያደረጋቸው ያሉ ማሻሻያዎች እና ኢኮኖሚያዊና እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግስትን በሀይል ለመለወጥ የሞከሩ የፖለቲካ ሀይሎችን አካሄድ ለመቀልበስ ተብሎ መታወጁን ተናግረዋል።

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲሁም የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታውጇል ብለዋል።

እርምጃው መወሰዱን ተከትሎ ሀገሪቱ ወደ ቀደመው ሰላሟ ተመልሳለች ሲሉም አብራርተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በ10 ቀናት ውስጥ በሁከቱ ከተሳተፉት ውስጥ 70 በመቶዎቹ በራሳቸው ፈቃድ ወደ ፀጥታ ሀይሉ በመቅረብ እጅ መስጠታቸውንና አስፈላጊውን ስልጠና እንዲወስዱ ከተደረገ በኋላ ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ማህበረሰባቸው ተቀላቅለዋል ብለዋል።

በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙትንም ትምህርት በመስጠት ወደ ህብረተሰቡ እንዲመለሱ የማድረጉ ሂደት መጀመሩን ጠቅሰው፥ ከታሰሩት መካከል የተወሰኑት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

መንግስት እያደረገ ባለው የማሻሻያ ስራዎች ተመጣጣኝ እና ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ማድረግ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት እና ኢኮኖሚውን እንደገና ማዋቀርን ያካተቱ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከስምንቱ የተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም የልማት ግቦች ሰባቱን አሳክታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ለተከታታይ አመታት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማምዝገብ የቻለች ሀገር ሆናለችም ሲሉም ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ከሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ክፍል እየተመዘገበ ካለው የኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፤ ይህ ደግሞ ወጣቱ ክፍል በሁከት እና ብጥብጥ ላይ እንዲሳተፍ አድርጎታል ብለዋል።

በሁከት እና ብጥብጡ ላይ ከተሳተፉት ውስጥም 99 በመቶው ወጣቱ መሆኑንና ከእነዚህም በብዛት እድሜያቸው ከ15 እስከ 30 ዓመት የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግስት ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

 

የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት ጋር በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ላይ፥ መንግስት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ እንዳለበት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ተረድቷል ብለዋል።

በተለይም ከዴሞክራሲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌደራል ኦዲተር ቢሮ፣ የፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም የመሰል ተቋማትን አቅም ለማሳገድ መንግስት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

እንደ አስፈላጊነቱም የምርጫ ህጉ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በቀጣይ የሚኖረው ፓርላማ ከዚህ ቀደም ውክልና ያላገኙ አካላትን ያካተተ እንደሚሆን ሙሉ ተስፋ አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ሃይለማርያም በማብራሪያቸው በኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ዙሪያ ባለፈው ዓመት ችግር ማጋጠሙን አንስተዋል፤ በዚህም ባለፉት 10 ዓመታት 8 በመቶ ሲያድግ የነበረው ግብርና እድገቱ ወደ 2 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማለቱን ነው ያነሱት።

ሆኖም ግን የኢንዱስትሪ ሴክተሩ በ20 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ በ11 በመቶ ማደጉ ሀገራዊ እድገቱ 8 በመቶ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው አጠቃላይ እድገትም 12 በመቶ እንደሚሆን እንጠብቃለን ሲሉም ነው የተናገሩት፤ በሀገሪቱ የተሻለ ዝናብ መገኘቱ ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር ያለውን ሚና በመጥቀስ።

የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት አለመቀነሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በማብራሪቸው አንስተዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አሁንም ቢሆን ከአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ፍሰቱ እንዳያስተጓጎል መንግስት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንዲቀጥሉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላቱ ዜጎቻቸውን እንዲያበረታቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የዘንድሮው የኢንቨስትመንት ፍሰት የተሻለ እንደሚሆን እንገምታለንም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አክለውም፥ በቀጣይ በሀገሪቱ የሚገነቡት 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግንባታቸው እየተካሄዱ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይም ምንም አይነት የግንባታ መቀዛቀዝ እንደማይስተዋልባቸው አስታውቀዋል።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED