የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን እንደሚገታ የህግ ባለሙያዎች ገለፁ

SelamAbesha.com

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን እንደሚገታ የህግ ባለሙያዎች ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2009

በሀገሪቱ የተከሰተውን ወቅታዊ አለመረጋጋት ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን የሚገታ ትከክለኛ እርምጃ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ተናግርዋል።

አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ ህግ ምሁራኑ፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመደበኛ የህግ አካሄድ ብቻ ሊገቱ የማይችሉ ህገወጥ ተግባራትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንስቃሴን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ ትክክለኛው ህጋዊ እርምጃ ነው ብለዋል።

 

ሌሎች ሀገራትም በወቅታዊነት ያጋጠማቸውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና የሽብር ስጋትን በዚህ መልኩ መቀነስ መቻላቸውን ነው ያነሱት።

የህግ ባለሙያ ዶክተር መንበረጸሃይ ታደሰ፥ ዋነኛውና ቅድሚያ የሚሰጠው የመንግስት ስራ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና ማረጋገጥ ነው ይላሉ።

በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት ዜጎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት ለማጥፋት እና የተረጋጋ ሰለማዊ እንቅስቃሴ ለመፍጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትክክለኛ እና ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቡን የሰላም ተስፋ መልሶ እንዲያለመልም እና እርግጠኝነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ ህገመንግስት አንቀጽ 93 መንግስት በሚከተለው መደበኛ አካሄድ ሊፈታቸው የማይችሉ ፈተናዎች ሲያጋጥመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይችላል ሲል የፈቀዳቸውን ጉዳዮች ይዘረዝራል።

የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፣ ህገመንግስታዊ ሰረአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥምና ይህን ሁኔታ በመደበኛ አካሄድ መፍታት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ፣ የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል የወረርሽኝ በሽታ ሲፈጠር፥ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነግግ ስልጣን ተሰጥቶታል።

የህግ ባለሙያው አቶ ዘፋንያ ዓለሙ፥ እነዚህ ሁኔታዎች ሁል ጊዜ የማያጋጥሙ እና ሲያጋጥሙም በቀላሉ ከውሳኔ ላይ የማይደረስባቸው ናቸው ይላሉ።

መንግስት መሰል ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ በእርግጥም የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን የሚያሳዩ ማሰረጃዎች መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ይህን መሰረት በማድረግ መንግስት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተስተዋለ ካለ ሁኔታ አንጻር ትክክለኛ ህጋዊ እርምጃ መሆኑን ነው አቶ ዘፋንያ የሚገልጹት።

በእንዲህ አይነት አስቸጋሪ ወቅቶች ላይ መንግስት አስቸኳየ ጊዜ አዋጅ ከመደንገግ ይልቅ በመደበኛ የህግ አካሄዶች ችግሮችን እፈታለው ብሎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ግን በመደበኛ ሁኔታ ላይ ያሉ ህጋዊ አካሄዶች በራሳቸው ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ነገሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ነው የሚሉት።

በእኛ ሀገርም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያልተለመደ በመሆኑ አዲስ ቢመስልም ሁሉም የአለም ሀገራት የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማቸው የሚደነግጉት መሆኑን ነው ዶክተር መንበረጸሃይ የሚገልጹት።

ሀገራቱ ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተከትሎ ያወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በወቅቱ ካካጋጠማቸው አለመረጋጋት እና ስጋት እንዲወጡ እንዳገዛቸው ነው አቶ ዘፋንያ የሚገልጹት።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED