የአልሲሲ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ፍሬ አልባ ሆነ

SelamAbesha.com

የአልሲሲ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ

ፍሬ አልባ ሆነ

የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ፍሬ አልባ ሆኖ ለትዝብት እየዳረጋቸው መሆኑ ተመለከተ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ነድፈው ቢንቀሳቀሱም ህልማቸው እውን ሊሆን አለመቻሉን ነው ኢንዲያን ኦሽን ኒውስ ሌተር በድረ ገፁ ያስነበበው ፡፡

ግብፅ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራውን ሽብርተኛ ቡድን በመደገፍ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ነድፋ የማይሳካ ህልም እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ድረ ገፁ አስታውሷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን ትችቱ ውሸት መሆኑን ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳሜህ ሹክሪ አዲስ አባባና አክራ ግብፅን የኦሮሞው አሸባሪ ቡድን(ኦነግ) ደጋፊ በማድረግ ትችት ማቅረባቸውን ለመተቸት ሞክረዋል፡፡ ግብፅ የዚህ ዓይነት ሽብርተኛን የመደገፍ ዓላማ የላትም በማለት፡፡

ራሳቸውን የቀጣናው የበላይ ለማድረግ የቃጣቸው ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኢትዮጵያና ቱርክ ‹‹ግብፅ ሽብርተኛ ቡድንን ትደግፋለች›› በሚል ያቀረቡት ትችት ከእውነታው የራቀ መሆኑን መናገራቸውን ድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ ሀብቷን አልምታ እንዳትጠቀም የሚሹ አካላት ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት ኃይሎችን በገንዘብ በመደገፍ አገሪቱን ለማተራመስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን መናገራቸውን ድረገ ገፁ አስታውሷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት ውጋት የሆነባቸው አካላት በተለያዩ መንገዶች የጥፋት በትራቸውን ለመሰንዘር ከመሞከር አለመቦዘናቸውን ኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ እየገለፀ እንደሚገኝም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ ግብፅ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ የላትም ቢሉም በተግባር ግን የሚታየው የዚህ ተቃራኒ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ለዚህም እአአ ከመስከረም 13 እስከ መስከረም 20 ቀን 2016 በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታ ስብሰባ ላይ የግብፅ ድብቅ ሴራ ተጋልጧል፡፡

በስብሰባው ላይ የግብፅ ባለሥልጣናት የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን ከጎናቸው በማሰለፍ የኢትዮጵያ ዕድገትና የልማት ግስጋሴን የሚገታ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ሲማፀኑ ተስተውሏል፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የናይጄሪያውን ፕሬዚዳንት መሀመድ ቡሀሪ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከጎናቸው ሆነው ለዕኩይ ድርጊታቸው እንዲተባበሯቸው ጠይቀዋል፡፡

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቃወሙና ግንባታው እንዲቆም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ፍላታቸውን አሳይተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በግብፅና ኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲነግስ ከማድረጉም በላይ ስጋት መሆኑን ለመሪዎቹ በመግልፅ የግድቡን ግንባታ እንዲቃወሙ ብርቱ ጥረት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በስብሰባው ላይ ለተሳተፉ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች ግብፅ በኦሮሚያ አካባቢዎች አመፅ እንዲነሳሳ እንደምትሰራ መልዕክት ሲልኩ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡

የግብፅ የኦሮሞ አሸባሪ ድርጅት(ኦነግ)ን የመርዳት ፍላጎት ፀሀይ የሞቀው ሀቅ መሆኑን መረጃው ማሳያዎችን በመጠቀስ ያስረዳል፡፡ የኦነግ አመራር የሆነው ኦምጊታ ሻሮ በግብፅ ዋና ከተማ ኑሮዉን ማድረጉን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡ ግለሰቡ በግብፅ መንግስት ጥገኝነት ከማግኘቱም በላይ የደህንነት ከለላ ይደረግለታል፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ ግብፅ ኢትዮጵያን የማተረማስ ስትራቴጂ የላትም እያሉ በድብቅ ግን የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ድብቅ ሴራ መሸረባቸው ክፉኛ እያስተዛዘባቸው እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED