SelamAbesha.com

                

የሊጉ አባላት አገሪቱን ለዛሬው እድገት ያበቁ ታጋዮችን ፈለግ በመከተል እንሰራለን አሉ

May 25,2016

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2008 አገሪቱን አሁን ለደረሰችበት ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ያበቁ ታጋዮችን ፈለግ በመከተል የስርዓቱ አደጋ የሆነውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለመዋጋት እንሰራለን ሲሉ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አባላት ገለጹ፡፡


ወጣቱ ትውልድ የስርዓቱ አደጋ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት በማክሸፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ነባር ታጋይ አቶ አባይ ፀሐዬ ጠይቀዋል፡፡


ወጣቶቹ ዛሬ በአዲስ አበባ የኢህአዴግ ወጣቾች ሊግ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ በፓናል ውይይት ላይ እንዳሉት ከ25 ዓመታት በፊት ወጣቱ ወደ ጦርነት በግዳጅ እየተገፋ ሲማገድበት የቆየ ስርዓት ነበር ፡፡


ይህን ስርዓት በመቃወም አብዛኛው ወጣት በስደትና በትግል ሜዳ የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት አሁን ያለው ትውልድ ከአገሪቱ ዕድገት በፍትሐዊነት እንዲጠቀም በር ከፍቶለታል ብለዋል።


ከሊጉ አባላት መካከል ወጣት አልማዝ ሐዱሽ እንደምትለው ሊጉ ከቀድሞው ታጋዮች ቁርጠኝነትና ለሕዝብ ጥቅም ቆሞ መታገልን መማር አለበት፡፡


በአሁኑ ወቅት ወጣቱ የደም መስዋእትነት ሳይሆን ለአገር እድገት ጠንክሮ መስራትንና የሚታዩ የመልካም አስተዳደር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ማክሰም ነው የሚጠበቅበት ብላለች፡፡


ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ታደሰ ታምር በበኩሉ ፓርቲው በትግል ወቅት ያሳለፈው ተጋድሎ አገር ተረካቢው ትውልድ ተስፋ ሳይቆርጥ ለእቅዱ ስኬት በጽናት መስራት እንዳለበት የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡


ፓርቲው በደማቅ ድል እየታጀበ እንዲቀጥል የወጣቱ ሚና ምትክ የሌለው ነው ያለው ወጣት ታደሰ አገሪቷ አሁን ያስመዘገበችውን እድገት ለማስቀጠልም ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርረን እንታገላለን ነው ያለው፡፡


ነባር ታጋይ አቶ አባይ ፀሐዬ ወጣቱ ትውልድ በተለይም የሊጉ አባላት የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት አደጋዎችን በማጋለጥ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡


በተለይም በወረዳና በዞን ያሉት አባላት በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የፍትሕና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል ደርሰው መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ተልእኳቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡


በትግሉ ወቅት ወጣቱ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን በማንሳት የከፈለው አኩሪ መስዋዕትነት ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እንዲመጣ ማስቻሉን ነው የገለጹት፡፡


"ኢህአደግ እንደ ፓርቲ ውጤታማ ሊሆን የቻለው በየወቅቱ የሚገጥሙትን ፈተናዎችና ተግዳሮች በመፍታትና ሕዝባዊ ውሳኔዎችን በማክበር ነው'' በማለት ገልጸው ይህንንም ወጣቱ ትውልድም ጠንክሮ ሊያስቀጥለው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡


የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ / የወጣቶች ሊግ በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።


Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED