SelamAbesha.com

                

ኮሚሽኑ ከአራት ሺህ 700 በላይ የፖሊስ አባላትና አመራሮች የእውቅና ሽልማት ሰጠ

Jun 23 2016

ደብረ ማርቆስ ሰኔ 16/2008 የፖሊስ አባላት የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው እንዲወጡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።


የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለበርካታ ዓመታት ለሰሩና በአገልግሎት ዘመናቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከአራት ሺህ 700 በላይ የፖሊስ አባላትና አመራሮች በደብረ ማርቆስ ከተማ የእውቅና ሽልማት ሰጥቷል።


ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በእዚሁ ወቅት እንዳሉት የፖሊስ አባላት የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው ሊወጡ ይገባል።


"የእውቅናና የሽልማት ሥርአቱ የፖሊስ አባላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ  በላቀ ትጋት እንዲሰሩ አደራ ይጥላል" ብለዋል።


አቶ ገዱ እንዳሉት፣ የፖሊስ ተቋሙም ሕዝባዊነቱን ጠብቆ  ከሕዝብ እና ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የሀገሪቱን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እሴቶች ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል።


የክልሉ ፖሊስ ኮሌጅ ምክትል ኮሚሽነር ጥበቡ ኃይሉ በበኩላቸው የፖሊስ አባላት ላለፉት ዓመታት የሕዝብና የመንግስትን ተልእኮ በንቃትና በሀገራዊ ስሜት ሲወጡ ቆይተዋል።


መንግስት ከእዚህ በፊት ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው የፖሊስ አባላቱና አመራሩ እስካሁን ለሰጡት ሙያዊ አገልግሎት ክብርና እውቅና ለመስጠት ሲባል ሽልማቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።


ከእውቅናና ክብር በተጨማሪ አባላቱ ለሙያው ከፍ ያለ ፍቅር ኖሯቸው እንዲሰሩ የማነሳሳት ዓላማ እንዳለው እስታውቀዋል።


በእውቅና ሽልማት ሥነስርአቱ ላይ ከ10 እስከ 25 ዓመት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት ከሪቫን እስከ ወርቅ ሜዳሊያና እንደአገልግሎት ዘመናቸው  ከሁለት እስከ አራት ወር ደመወዛቸው በሽልማት ተበርክቶላቸዋል።


ከተሸላሚ የፖሊስ አባላት መካከል ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።


ለሽልማት ከበቁት መካከል የወርቅ ሜዳሊያና የአራት ወር ደመወዛቸውን የተሸለሙት የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ መምህር ኮማንደር ፈንታሁን አለሙ መንግስት የፖሊስ ሠራዊቱን ሥራና ልፋት ተገንዝቦ ክብር መስጠቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።


በቀጣይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በበለጠ በመወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ለህገመንግስቱ ዘብ ሆኖ የሚያገለግል ዜጋ ለማፍራት ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።


የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር እንየው ዘውዴ  በበኩላቸው ሽልማቱ የጀግንነት ኩራት እንደሰጣቸው ገልጸዋል።


"የፖሊስ ሥራ ለሕዝብ ችግር መድረስ በመሆኑ ይህን ተግባር አጠናክሬ እንድሰራ  ሽልማቱ ከፍተኛ ወኔ ፈጥሮልኛል" ብለዋል።


ቀጣይ ወደተቋሙ በሚመጡ ወጣቶች ላይ የሥራ ፍቅር የሚያሳድር በመሆኑም ተጠናክሮ መቀጥል እንዳለበት ተናግረዋል።


በሽልማት ሥነ ስርአቱ ላይ የኦሮሚያ፣ የትግራይና የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከፌደራል መካላከያ ሠራዊትና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ እንግዶች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።


Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED