ከህዳሴው ግድብ 750 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ የሚያስገኙት ተርባይኖች ገጠማ ይጀመራል

SelamAbesha.com

ከህዳሴው ግድብ 750 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ የሚያስገኙት ተርባይኖች ገጠማ ይጀመራል

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት የሚያስችሉት ተርባይኖች ገጠማእንደሚጀመር የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት አስታወቀ ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አሰተባባሪና የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ምክርቤቱ ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንዳስታወቁት ፤ ተርባይኖቹ ወደ ግድቡ ስፍራ በመድረሳቸው በቅርቡ ተከላ ይጀመራል ።

ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ28 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከመላ የሀገሪቱ ህዝቦች መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል።

የግንባታ ስራው 54 በመቶ የደረሰው ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ቃል ከተገባው 49 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከግማሽ በላይ መሆኑን አመልክተዋል ።

በ2008 በጀት ዓመት 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ቃል ተገብቶ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን የተሰበሰበበት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የተሰበሰበበት ዓመት መሆኑንም ጠቁመዋል ።

ከዲያስፖራው ማህበረሰብም እስካሁን 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ በጉባኤው ላይ አንስቷል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ለግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉም ገልጸዋል።

የውሃ ፍሰቱን ወደ ዋናው ግድብ አቅጣጫ የሚያመጣው የሳድል ግድብ ስራ መሰራት ካለበት 15 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአለት ሙሌት ውስጥ 8 ሚሊዮን ያህሉ መከናወኑ ተነስቷል ።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም በበኩላቸው የግድቡን ስራ ለማስተጓጎል በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ጽንፈኛ ሀይሎች ጋር የሚተባበሩ የግብጽ ጽንፈኛ ተቋማትን የግብጽ መንግስት ከድርጊታቸው እንዲያስቆማቸው ኢትዮጵያ ማሳሰቧን ገልጸዋል (ኤፍ.ቢ.ሲ) ።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED