SelamAbesha.com

                

ኢትዮጵያና ኬንያ ተፎካካሪ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ አገራት በመሆናቸው ለጋራ ስኬት ሊሰሩ ይገባል-ፕሬዝዳንት ኬንያታ

Jun 23 2016

ናይሮቢ ሰኔ 17/2008 ኢትዮጵያና ኬንያ ተፎካካሪ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ አገራት በመሆናቸው ለጋራ ስኬት ሊሰሩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናገሩ።


የኢትዮ-ኬንያ የቢዝነስ ፎረም ትናንት ምሽት በናይሮቢ ተካሂዷል።


ኢትዮጵያና ኬንያ በጥቅሉ 150 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ፣ ሰፊ የተፈጥሮ ኃብትና በፈጣን ዕድገት የታጀበ የግብርና ኢኮኖሚ ያላቸው አገራት ናቸው።


አገራቱ 650 ሚሊዮን ሕዝብ ያካተት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል መሆናቸው ደግሞ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ተጨማሪ ዕድሎችን የሚያስገኝ ነው።


ለዘመናት ዝቅተኛ የነበረው በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ ንግድ አሁን አሁን እያደገ መምጣቱ ለአሕጉራዊ ልማቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አድርጎታል።


ኢትዮጵያና ኬንያም ድንበር ተሻጋሪ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር በሚል ነው በናይሮቢ ከንግድ ማኅበረሰቦች ጋር የቢዝነስ ፎረም ያካሄዱት። 


በፎረሙ የተገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ኬንያ ተፎካካሪ አገራት ተደርገው መታየት የለባቸውም።


ይልቁንም አገራቱ የጋራ ግብና መድረሻ ያላቸው በመሆናቸው እርስ በእርስ በመደጋገፍ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ውድድሩን በብቃት ለመወጣት የሚሰሩ ናቸው። 


ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያና ኬንያ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተቀናጀተው መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ነው ፕሬዝዳንት ኬንያታ የተናገሩት።


እናም የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነውን የግሉን ዘርፍ የዕድገት ስኬት ለማረጋገጥ በአጋርነት መሥራት እንደሚጠበቅ ነው ያስገነዘቡት።


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት በዕውነተኛ ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው።


ሰሞኑን በኬንያ የተካሄደው 35ኛው የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም ይህን ትብብር በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ብለዋል።


"ኢትዮጵያና ኬንያ ተፎካካሪ ሳይሆኑ ተደጋጋፊ ናቸው" የሚለው ሀሳብ በኢትዮጵያ በኩልም ተቀባይነት ያለው እንደሆነ አስምረውበታል።


"ሁለቱ አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው አቅም የተወሰነ በመሆኑ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ አብረው መሥራት ይኖርባቸዋል" በማለት የትብብሩን አስፈላጊነት ገልጸዋል።


ከዚህ አንፃር የኢትዮ-ኬንያ የንግድ ማኅበረሰቦች ጤናማ የሆነ ድንበር ተሻጋሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለመፍጠር ተነሳሽነቱን ወስደው መስራታቸውን አወድሰዋል።


ቀጣናዊ የንግድ ትስስሩን ለማጠናከርም የኢትዮ-ኬንያ-ደቡብ ሱዳን የመሰረተ ልማት ኮሪደርን በተፋጠነ ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ተናግረዋል።


የሁለቱ አገራት ባለኃብቶች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በሽርክና እንዲሰሩ ማበረታታት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።


የኬንያ የግሉን ዘርፍ በመወከል ንግግር ያደረጉት ፍሎራ ሙታሂ እንደገለጹት የንግዱ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይፈልጋል።


በተለይም በብረታ ብረት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በግብርና፣ በአይሲቲ፣ በግንባታ ግብዓቶች፣ በሻይ ቅጠል፣ በምግብ ዘይት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በጫማና በቆዳ ንግድና ኢንቨስትመንቱን የማጎልበት ፍላጎት አለው።


ይህን እውን ለማድረግ የሁለቱ አገራት መንግሥታት የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን በማፋጠን ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑትን ጉዳዮች በጋራ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ አሕጉራዊ ዕድገቱን በማቀጣጠል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።


ከዚህ አኳያ አሕጉራዊ የግሉ ዘርፍ የእርስ በእርስ አጋርነትን በማጎልበት ለአፍሪካ ዕድገት ከዚህ በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል።


የኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ የቆንስላ ጀነራል ጽህፈት ቤት በናይሮቢ በመክፈት ነበር።


እንዲያም ሆኖ ሁለቱ አገራት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው የንግድ ልውውጥ ያን ያህል አይደለም።


እንደ ጎርጎሮሳውያን የጊዜ ቀመር በ2012 ኢትዮጵያና ኬንያ ልዩ የስምምነት ማዕቀፍ በመፈረም በሁለቱም አገራት የንግድ እንቅስቃሴን የሚያሳልጡ ወኪል ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖራቸው ተደርጓል።


ስምምነቱ ሁለቱ አገራት እንደ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማት፣ የምግብ ዋስትና፣ ተደራራቢ ግብርን በማስቀረት ባሉ ቁልፍ መስኮች የትብብር ማዕቀፍ የሚፈጥር ነው።


ኢትዮጵያና ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የንግድ ቀጣና የታቀፉ በመሆናቸው የእርስ በእርስ ትስስራቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው በፎረሙ በስፋት ተነስቷል።


የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴ ትስስሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በአሃዝ አስደግፈው አብራርተዋል።


በአሁኑ ጊዜ 275 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስመዘገቡ 83 የኬንያ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ እንደሚገኙም ተናግረዋል።


ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤናና ማኑፋክቸሪንግ ደግሞ ኬንያውያን ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ናቸው።


የሁለቱ አገራት የንግዱ ልውውጥም ባለፉት አሥር ዓመታት ፈጣን ዕድገት ማሳየቱን ነው አቶ አያና የተናገሩት።


ይህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 ከነበረው 24 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል።


በውጭ ንግድ ረገድ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት መጠን በ2006 ከነበረው 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በ2015 ወደ 21 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረዋል።


በአንፃሩ ኬንያ በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ልካ ታገኝ ከነበረው 24 ሚሊዮን ዶላር ወደ 39 ሚሊዮን ዶላር ማሳደግ ችላለች።


ዕድገቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በሁለቱ አገራት መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።


ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ፀረ-ነፍሳት መድኃኒት፣ ብረት፣ አልሙኒየም፣ የህክምና መሣሪያዎች፣ የቤት ቁሳቁሶች ስትልክ ከኢትዮጵያ ደግሞ አትክልት፣ ቅመማ ቅመም፣ የቅባት እህሎች፣ ኖራ፣ ሲሚንቶ፣ የፋብሪካ ውጤት የሆኑ የግንባታ ዕቃዎች፣ ጥራጥሬና የአትክልት ዘይት ታስገባለች።


 


Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED