ኢትዮጵያና ሞሮኮ በ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተስማሙ

SelamAbesha.com

ኢትዮጵያና ሞሮኮ በ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተስማሙ

ህዳር 10፣ 2009

ኢትዮጵያና ሞሮኮ በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር የመጀመሪያ ምዕራፍ የተቀናጀ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

ሁለቱ አገሮች በጋራ ሊሰሩባቸው ባሰቧቸው ሌሎች 13 ዋና ዋና የልማት መስኮችም የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

 

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሞሮኮ ንጉስ መሓመድ ስድስተኛ፣ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና ጠቅላይ ሚነስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ነው የመግባቢያ ሰነዶቹ የተፈረሙት።

በውኃ አያያዝና በመስኖ ልማት ዘርፍ፣ የሁለትዮሽ ቢዝነስ ምክር ቤት ለመመስረትና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶች ከተፈረሙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

 

የመሠረታዊ የነዳጅ ምርት፣  የኢንዳስትሪ ፓርኮች ሎጂስቲክ አቅረቦት፣ የሳይንስ፣ ቴክኒክና ባህል ትብብር፣ የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት፣ የንግድ ዘርፍ እድገትና ተደጋጋሚ ታክስን ለማስቀረት የተደረጉ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው።

 

የመሠረታዊ የነዳጅ ምርት፣  የኢንዳስትሪ ፓርኮች ሎጂስቲክ አቅረቦት፣ የሳይንስ፣ ቴክኒክና ባህል ትብብር፣ የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት፣ የንግድ ዘርፍ እድገትና ተደጋጋሚ ታክስን ለማስቀረት የተደረጉ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው። 

 

ሁለቱ አገሮች በኢንቨስትመንት ማስፋፋትና ጥበቃ፣ በግብርና ዘርፍ በጋራ ለመስራትና በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ተባብረው ለመስራት በሚያስችላቸውና በሌሎች ጉዳዮች የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።

 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በአገሮቹ መካከል የተደረጉት ስምምነቶች ኢንቨስተመንትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጥራሉ።

 

በድሬደዋ ኢንዳስትሪ ፓርክ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የተደረገው ስምምነት እንደሚያመለክተው፤ ፋብሪካው እኤአ በ2022 ዓ.ም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።  በዚያን  ወቅት እሰከ 80 በመቶ ድረስ ምርት ለማምረት ይችላል።

 

ይሄው ፋብሪካ እኤአ በ2025 ዓ.ም ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፍላጎቷን ሙሉ በሙሉ በራሷ አቅም ለመሸፈን እንደሚያስችላትም ተጠቁሟል።

 

ኮሚሽነር ፍጹም፤ ብዙ ጥናት ሲካሄድበት የቆየው የማዳበሪያ ፋብሪካው ለአገሪቷ  ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማዳን እንደሚያስችል ተናግረዋል።

 

በአገሪቷ ለማዳበሪያ ምርት የሚያገለግሉ እንደ ፖታሽ የመሳሰሉ ጥሬ እቃዎች መኖራቸው መልካም አጋጣሚ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ''ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ፍላጎትን በማሟላት ወደ ውጪ ለመላክ ጥረት ይደረጋል'' ነው ያሉት።

 

ኦ.ሲ.ፒ የተባለው ፋብሪካውን የሚገነባው ኩባንያ ተወካይ ፋይከል ቤናሙር በበኩላቸው፤ የፋብሪካው አዋጭነት ጥናት መጠናቀቁን ገልጸው፤ "በቅርቡ ግንባታው ይጀምራል" ብለዋል።

 

የፋብሪካውን ግንባታው  ፋብሪካው እኤአ ከ2022  ጀምሮ በዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ቶን ማዳበሪያ ማምረት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

 

ፋብሪካው በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ "የምርት አቅሙን በዓመት ወደ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ቶን ያሳድጋል" ያሉት ተወካዩ፤ ግንባታውም የመጀመሪያው ምዕራፍ እንደተጠናቀቀ እንደሚጀመር ነው የተናገሩት።

 

ሁለቱ አገሮች በእንዲህ አይነት መልኩ አብረው መስራታቸው አዳጊ አገራት እርስ በርሳቸው የሚተጋገዙበት የደቡብ ለደቡብ ትብብር ማሳያ መሆኑም ተመልከቷል።

 

ምንጭ፡- ኢዜአ

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED