ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነት ትግበራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ሀገራት በማሳተፍ መከናወን አለበት የሚል አቋም ይዛለች

SelamAbesha.com

ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነት ትግበራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ሀገራት በማሳተፍ መከናወን አለበት የሚል አቋም ይዛለች

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2009 የፓሪሱ ስምምነትና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው 22ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የመከራከሪያ ርእስ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን የፓሪስ ስምምነት ትግበራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ሀገራት ባሳተፈ መልኩ መከናወን አለበት የሚል አቋም ይዟል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴታ አቶ ቃሬ ጫዌቻ ኢትዮጵያ የራሷንና የወከለቻቸውን ሀገራት ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ የድርድር ሃሳብ እያቀረበች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ሀገራት ፎረም ፕሬዚዳንት እንደመሆኗ፥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንዲተገበሩና ዘላቂነት ያለው ድጋፍ እንዲኖር ለማስቻል ከአባል አገራቱ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ማስታወቋ ይታወሳል።

በመሪነት ጊዜዋ ሁሉን አቀፍ አማራጮችን በመጠቀም ለፎረሙ አስፈላጊውን ድጋፍ የማሰባሰባሰብና የፎረሙን ድምፅ ተሰሚነት ለማረጋገጥ እንደምትሰራም ተገልጿል።

ሀገሪቷ የራሷንና የወከለቻቸውን ሀገራት ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ የድርድር ሃሳብ እያቀረበችውም ለዚሁ እንደሆነም ተገልጿል።

በሌላ በኩል በፓሪሱ ስምምነት ላይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያድረጉ ከስምምነት መደረሱ የሚታወስ ነው።

አሁን ላይ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠው ገንዘብ መጠን እና የሀገራት መዋጮ እንዴት ይከፋፈል የሚለው ጉዳይም የማራካሹ ጉባኤ ላይ መናጋገርያ ሆኗል።

እስከ ቅዳሜ ይቀጥላል ተብሎ በሚጠበቀው ጉባኤ ላይም በዚህ ላይ ከውሳኔ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በሞሮኮ ዋና ከተማ ማራካሽ እየተካሄደ ያለው 22ኛው አለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ከ40 በላይ የመንግስት እና ከ30 በላይ የሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ክፍል የተወጣጡ ከ30 ሺህ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችም በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ነው።

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED