SelamAbesha.com

                

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃይል ልትሸጥ ነው

August 26, 2016

አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2008 ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን ህዝብና መንግሥት ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።


በደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ሚሊዮኖች መፈናቀላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።


ለችግሩ እልባት ለማበጀት የሚደረገው ጥረትም መፍትሄ ሳያመጣ እስካሁን እንደቀጠለ ነው።


በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የጥምር መንግሥት ምስረታ ስምምነት በመቶዎች የሚቆጠር ሕይወት በቀጠፈው የጁባ ግጭት ተኮላሽቷል።


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል።


የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ዳግም ያገረሸውን ግጭት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች።


የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) መሪዎች የደቡብ ሱዳንን ህዝብና መንግሥት ሰላምና ደህንነት ለማስከበር እንዲያግዝ በቅርቡ አካባቢያዊ የሠላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።


ውሳኔውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድጋፍ አግኝቷል።


እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገርም ሆነ እንደ ኢጋድ ሊቀ-መንበርነቷ አካባቢያዊ የሠላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ታደርጋለች።


“አካባቢያዊ የሠላም አስከባሪ ኃይል ለማደራጀትም ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።


በሌላ ዜና በሳምንቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሲንጋፖር ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።


የሚኒስትሩ ጉብኝት የኢትዮጵያና የሲንጋፖርን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ዙሪያ መምከር ሲሆን ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ያላትን አማራጭ ለማስተዋወቅ ዕድል የሰጠ መድረክ እንደነበር ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። 


ሁለቱ አገራት በወጪና ገቢ ምርቶቻቸው ላይ ተደራራቢ የታክስ ሥርዓት የሚያስቀር ስምምነት ፈጽመዋል።


በስምምነቱ ሲንጋፖር ከኢትዮጵያ ጋር ተደራራቢ የታክስ ሥርዓትን በማስወገድ ለባለሃብቶች አስተማማኝ የስራ አካባቢ ለመፍጠርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ነው።


ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶክተር ቴድሮስ በአፍሪካ ልማት ላይ ትኩረቱን በሚያደርገው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ኬኒያ ናይሮቢ ይገኛሉ።


ጉባኤው አፍሪካ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያጋጠሟትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል



Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED