ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ልትሸጥ ነው

SelamAbesha.com

ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ልትሸጥ ነው

 

 

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 20፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ልታደርግ ነው።

 

የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ እንደገለጹት፥ ሁለቱ አገሮች የሽያጭ ስምምነቱን በሚቀጥሉት ሳምንታት ያከናውናሉ።

 

 

ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል በኬንያ በኩል የሚያልፍ በመሆኑ በኬንያና ታንዛንያ መካከል የሚደረግ ስምምነትም እንዳለ ተናግረዋል።

 

 

ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ገዝተው መጠቀም የጀመሩት ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያም ተጨማሪ ኃይል መጠየቃቸውን ነው ኢንጅነር አዜብ የገለጹት።

 

 

አገራቱ ከውድና አካባቢን ከሚጎዳ የሃይል አጠቃቀም ይልቅ ኢትዮጵያ የምታመርተውን ታዳሽ ኃይል ለመጠቀም ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

 

በቀጣይ ሀገራቱ የጠየቁትን የኃይል ፍላጎት ለማቅረብ ተጨማሪ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመሥራት ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

 

 

200 ሜጋ ዋት ኃይል ፍላጎት ላላት ኬንያ ኃይል ለመስጠት የመስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ተፈርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።

 

 

ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት እያቀረበች ያለችው የኤሌክትሪክ ኃይል የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከርና የልማት ትስስሩን በማፋጠን ላይ ይገኛል።

 

 

ግንባታው በቅርቡ የተጠናቀቀውና 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ጊቤ ሦስት ሃይል ማመንጫ አሁን ላይ 900 ሜጋ ዋት እያመነጨ ነው።

 

 

በአሁኑ ወቅት ጊቤ ሦስትን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉት ግድቦች የሚያመነጭቱን አቅም ለመጠቀም የሚያስችል የሃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ጣበያዎችን አቅም የማሳደግና አዲስ የመዘርጋት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

 

 

ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት የምታቀርበው ኃይል እንደሚጨምር ይጠበቃል።

 

 

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ባሻገር ሩዋንዳና ቡሩንዲ ለመሳሰሉ በጣም ውድና ታዳሽ ያልሆነ ኃይል ለሚጠቀሙ አገራት እንዲሁም ለሰሜን አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የማቅረቡ ዕቅድ አላት።

 

 

ታንዛንያ ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ በመቀጠል ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል የምታገኝ አራተኛዋ አገር ትሆናለች።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED