ኢትየጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያካሂዱት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ለመፈራረም ተቃርበዋል

SelamAbesha.com

ኢትየጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያካሂዱት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ለመፈራረም ተቃርበዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትየጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያካሂዱት ሁለት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ለመፈረም ተቃርበዋል።

 

የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ከኩባንያዎቹ ጋር የኮንትራት ውል ለማሰር የሚያስችል ሰነድ ላይ ሶስቱ ሃገራት ከስምምነት እየደረሱ ነው።

 

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ፍሰት እና ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽኖ ላይ ጥናት እንዲሰሩ ቢ አር ኤል እና አርቴሊያ የተባሉ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች መመረጣቸው ይታወሳል።

 

ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ፥ አሁን ላይ ጥናቱን ለማስጀመር ከሁለቱ ኩባንያዎች ጋር የሚፈርሙት ሰነድ ዝግጅት ወደ መገባደዱ ተቃርቧል ነው ያሉት።

 

በአሁኑ ጊዜም ሶስቱ ሀገራት ለመጠናቀቅ እየተቃረበ ባለው ስነድ ላይ በተለያዩ ጊዜያት እየተወያዩ ጥናት ማስጀመርያ የመጨረሻ ፊርማን ለማኖር መቃረባቸውን ተናግረዋል።

 

የጥናቱ ማስጀመርያ ቀን በትክክል አልታወቀም ያሉት አቶ ሞቱማ፥ ቀኑን ቆርጦ ጥናቱን ማስጀመር የሶስቱም ሀገራት ውሳኔ ነው፤ ከተደረጉ ውይይቶች መረዳት የተቻለው ግን በቅርቡ ጥናቱ እንደሚጀመር ነው ብለዋል።

 

በሌላ በኩል የሁለቱ ጥናቶች ውጤት ምንም ይሁን ምንም በሀገራቱ ላይ የአስገዳጅነት ውጤትን አያመጡም ሲሉም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

 

ሀገራቱ እየተወያዩባቸው ያሉ ጉዳዮችን እያከበሩ ነው ያሉት አቶ ሞቱማ፥ ይህም ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍላጎቷን የማሳየቷ ውጤት ነው ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር በዚህ መልክ የመጣውን መቀራረብ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ስራዋን አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያሉት።

 

ይህም ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ትልቅ ድል መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የሚያነሱት።

 

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ የውሃ አያያዝ እና አለቃቀቅ፣ ሀይድሮሎጂካል ሲሚዩሌሽን ሞዴል እና ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተጽእኖ እንዲጠና ከዓመት በፊት መስማተታቸው ይታወሳል።

 

ለዚህም ጥናቱን የሚያከናውኑ ኩባንያዎችን መረጣ የተካሄደ ሲሆን፥ ቀድሞ የፈረንሳዩ ቢ.አር.ኤል እና የሆላንዱ ዴልታሬዝ የተመረጡ ቢሆንም፤ ዴልታሬዝ ከቢ.አር.ኤል ጋር መግባባት ባለመቻሉ በሌላኛው ፈረንሳዊ ኩባንያ አርቴሊያ መተካቱ አይዘነጋም።

 

ሁለቱ ኩባንያዎች ጥናቶቹን በ70/30 ክፍፍል የሚያከናውኑ ሲሆን፥ 70 በመቶው የጥናቱ ክፍል በቢ.አር.ኤል 30 በመቶው ደግሞ በአርቴሊያ ነው የሚከናወነው።

 

የሶስቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ከሁለቱ ኩባንያዎች የቀረበላቸውን የጥናት እቅድ ተስማምተው ተቀብለዋል።

 

ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጥናቱን ሲያከናውኑ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የሚከፈላቸው ሲሆን፥ ወጪው በሶስቱ ሀገራት እኩል የሚሸፈን ነው።

 

ኩባኒያዎችም ወደ ስራ ከገቡ በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ ሁለቱን ጥናቶች አጠናቀው ለሃገራቱ ያቀርባሉ።

 

ኢትዮጵያ ቀድሞ በራሷ ሁለቱንም ጥናቶች ያከናወነች በመሆኑ በሁለቱ ጥናቶች የተለየ ውጤት ይመጣል ተብሎ አይጠበቀም፤ የጥናቶቹ አላማ መተማመን ለማምጣት ነው ብላ ታምናለች።

 

 

በበላይ ተስፋዬ

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED