አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ተሾሙ

SelamAbesha.com

የሰንደቅ ዓላማ ክብርን መጠበቅ እንደሚገባ ተመለከተ

 

ባህር ዳር/ደሴ ጥቅምት 7/2009 ሰንደቅ ዓላማ ለሀገሪቱ ያስገኘውን ጥቅምና ፋይዳ በመገንዘብ ሁሉም ሊያከብረውና ሊጠብቀው እንደሚገባ  የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አመለከቱ።

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር መንግስት ሠራተኞች በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ዜጎች ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እንዲገልጹ እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ሠራተኞችና ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ አካላት ዘጠነኛውን የሰንደቅ አላማ ቀን ዛሬ በፓናል ውይይትና ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል አክብረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት፣ የዓለም ሀገሮች የራሳቸውን ማንነትና ሉዓላዊነት ለመግለጽ ሰንደቅ ዓላማን በምልክትነት ሲጠቀሙ ይታያል።

ኢትዮጵያም የራሷን ሰንደቅ ዓላማ በማዘጋጀት ለነጻነቷ፣ ለአንድነቷና ለክብሯ ማስጠበቂያ የትግል ዓርማ አድርጋ ስትጠቀም የኖረች ሀገር ናት።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅረው እንዲኖሩ፤ የሃይማኖትና የቋንቋ ዕኩልነት እንዲሰፍን መሰረት የተጣለውም በሰንደቅ ዓላማው ስር በመሰባሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን አንድነትና አብሮ የመኖር ስሜት በማጎልበት ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ሥር እየሰደደ እንዲመጣ በቀጣይ ስለሰንደቅ ዓላማ ክብር ለትውልዱ ማስተማርና ማስረጽ ያስፈልጋል።

ሰንደቅ ዓላማ ለሀገሪቱ ያስገኘውን ጥቅምና ፋይዳ በመገንዘብ ሁሉም ሊያከብረውና ሊጠብቀው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ 

"በዓሉን ዛሬ ስናከብር የማንነታችን መገለጫ የሆነውን አርማችንን በማስታወስና በዓመቱ የተሻለ የልማት ሥራ ለማከናወን መዘጋጀታችንን ቃል በመግባት መሆን አለበት" ብለዋል።

"ሰንደቅ ዓላማ በሀገራችን ያሉ ሁሉን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት የዘለቀ አንድነትና ጥንካሬ የሚያሳይ ነው" ያሉት ደግሞ ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ጉግሳ መሸሻ ናቸው።

"ለጥቁሮች ተጋድሎና ነጻነት ፋና ወጊ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ አርማችንን በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ቀለማቱን በመውሰድ የራሳቸው አርማ እንዲሆን ማድረጋቸው ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኩራት መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።

ወይዘሮ ፋጡማ አደም የተባሉ እናት በበኩላቸው "ሰንደቅ አላማ ሴቶችን ከጭቆና ያላቀቀ፤ የሃይማኖት ዕኩልነትን ያስከበረ የአንድነታችን መገለጫ አርማችን በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ልንጠብቀው ይገባል" ብለዋል።

ለልጆቻቸው የሰንደቅ አላማን ምንነት፣ ጠቀሜታና ክብር አውቀው እንዲያድጉም የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የፓናል ውይይቱ ታዳሚና የክልሉ ልዩ ኃይል የፖሊስ አባል  ኮንስታብል ያረጋል ተስፋነው በበኩሉ "አባቶቻችን ለነጻነት ሲሉ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሰንደቅ አላማችንን  ለእኛ አስረክበውናል።"

በአደራ የተረከበውን ሰንደቅ አላማ በተሰለፈበት የሥራ መስክ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል።

"ሰንደቅ ዓላማችን የሉዐላዊነታችን መገለጫ፤ በብዝሀነታችን ላይ ለተመሰረተው አንድነታችን ዓርማ ነው!"በሚል መሪ ቃል የተከበረው 9ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በምክር ቤቱና በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች ሠራተኞች በፓናል ውይይት አክብረው መዋላቸው ታውቋል።

በተመሳሳይ ዜና የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ዜጎች ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እንዲገልጹ እድል የሚሰጥ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር መንግስት ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡

"ሰንደቅ ዓላማችን የሉአላዊነታችን መገለጫ፤ በብዝሀነታችን ላይ ለተመሰረተው አንድነታችን ዓርማ ነው" በሚል መሪ ቃል ዘጠነኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ሠራተኛ አቶ ኃይሉ መንገሻ በአካባቢው ከ70 ዓመት በላይ የዘለቀ ሰንደቅ አላማን በክብር የመስቀልና የማውረድ ተሞክሮ እንዳለ ተናግረዋል።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ ወጣቱ ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ፍቅር እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን እንዲያከበር እድል ይሰጠዋል።

ሰንደቅ ዓላማ የማንነታችን መገለጫ በመሆኑ በአንዳንድ የመንግስት መስሪያቤቶች ባንዲራ በአግባቡ የማይሰቀልበትና የማይወርድበት ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የዞኑ አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ባልደረባ አቶ ተስፋዬ አሻግሬ በበኩላቸው በሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፈተቶችን ለመዝጋት አስከ ቀበሌ ድረስ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሀን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  እንደገለጹት፣ ሰንደቅ አላማ የብሔራዊ ኩራት ተምሳሌት፣ የህግ የበላይነት መገለጫ፣ የአገርና የህዝብ ፍቅር ማሳያ ነው።

በአድዋ ጦርነት ውቅት የጣሊያንን ጦር ድል ነስቶ በመመለስ፣ ሶማሊያ አገራችንን በወረረችበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ጀግኖች የብሔራዊ ኩራትና የአትንኩኝ ባይነት ምንጭ በመሆን፣ በሻአቢያ ወረራም ጠላትን ድባቅ በመምታት ኢትዮጵያ በዜጎቿ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ሰንደቅ ዓላማ ያደረገው ተጽዕኖ የላቀ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እንደ  አቶ ብርሃኑ ገላጻ አያት ቅድመ አያቶች ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሕይወታቸውን እንደከፈሉ ሁሉ ይሄ ትውልድም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ዘጠነኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የደሴ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች፣ አመራሩ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌ ተወካዮች በተገኙበት በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED