አሸንዳ-ልጃገረዶች ደምቀው የሚታዩበት ባህላዊ በዓል

SelamAbesha.com

አሸንዳ ---ልጃገረዶች ደምቀው የሚታዩበት ባህላዊ በዓል

መቀሌ ነሃሴ 17/2008 በትግራይ ክልል በድምቀት ከሚከበሩ ባህላዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው - የአሸንዳ በዓል። በዓሉ ልጃገረዶች በየዓመቱ በጉጉትና በአንድነት ተሰባስበው የሚያከብሩት በዓል ሲሆን የሴቶች የነጻነት በዓል ተደርጎም ይወሰዳል።

 

በዓሉ ከትናንት ጀምሮ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው መቀሌ በመከበር ላይ ነው። በተለያዩ ሕብረ ቀለማት በተሽቆጠቆጡ አልባሳት፣ ጌጣጌጥና በተለየ የፀጉር አሰራር የተዋቡ በርካታ ልጃገረዶች ወደበዓሉ ሥፍራ በመምጣት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተውታል።

 

በዓመት አንዴ በሚከበረው በእዚህ በዓል ላይ ልጃገረዶች እጅግ አምረውና ደምቀው ነው የመጡት። በአለባበሳቸው፣ በሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች፣ በጭፈራቸውና በእንቅስቃሴያቸው የሁሉም ቀልብ ያርፍባቸዋል።

 

ከትናንት ጀምሮ ለአራት ቀናት እየተከበረ ባለው የአሸንዳ በዓል ላይ በርካታ ልጃገረዶችንና ሴቶችን ጨምሮ የፌደራልና የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ቱሪስቶችና የተለያዩ እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል።

 

በበዓሉ መክፈቻ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ እንዳሉት፣ ልጃገረዶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣውን የአሸንዳ በዓል ጠብቀውና ተንከባክበው ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል።

 

እርሳቸው እንዳሉት በዓሉን በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በመንግስት በኩል ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

 

"በዓሉ የሰላምና የፍቅር መሰረት ነው ያሉት " ሚኒስትሯ፣ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከሴቶች በተለይም ከክልሉ ልጃገረዶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 

በአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች በተለያዩ ሕብረ ቀለማት በተሽቆጠቆጡ አልባሳት ደምቀውና በተለያዩ ጌጣጌጦች ተውበው ማየት እንደሚያስደስት ገልጸው፣ "እንዲህ ያለው አኩሪ የባህል ቱርፋት ተጠብቆ እንዲቆይ በመንግስት በኩል ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

 

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው፣ በክልሉ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

 

አቶ ዳዊት እንዳሉት፣ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ለክልሉ የገቢ ምንጭና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

 

ከአሥር ዓመታት በኋላ በዓሉን ለማክበር ከነበረችበት አረብ አገር ወደ አካባቢው መምጣቷን የገለጸችው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት አበባ ጸጋይ በበኩሏ፣" በቴሌቭዝን ብቻ ስመለከተው የነበረውን በዓል በአካል በመገኘትና የበዓሉ ታዳሚ በመሆን በማክበሬ ኩራትና ደስታ ተሰምቶኛል" ብላለች።

 

በቀጣይም በዓሉን በምትኖርበት የዓረብ ሀገር ለማስተዋወቅ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ነው የገለጸችው።

 

የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አጸደ አብርሃ ፣ "የአሸንዳ በዓል የሴቶች የነጻነት በዓል ተደርጎ ይቆጠራል" ብለዋል፣ በዓሉ በመንግስት የተለየ ትኩረት አግኝቶ በመከበሩም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

 

ወጣት ልጃገረዶችም ከወላጆቻቸው የተረከቡትን በዓል ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED