ብዝኃነት በአግባቡ ከተያዘ ውበት ነው ሚኒስትር ካሳ ተክለብርሃን

SelamAbesha.com

ብዝኃነት በአግባቡ ከተያዘ ውበት ነው''-ሚኒስትር ካሳ ተክለብርሃን

Jun 23 2016

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2008 “በአገሪቱ በመነጋገርና በመወያየት የሚያምን ትውልድ ይዘን ብዝሃነት ውበት የማይሆንበት ምክንያት የለም" ሲሉ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናገሩ።

 

ሚኒስትሩ ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “የሰላም ክለብ “ባዘጋጀው መድረክ ''ብዝኃነትና አንድነት የአገሪቱን ሰላም ለማስቀጠል ያላቸው ፋይዳ'' በሚል ርዕስ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

 

የክለቡ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ብዝሃነትና አንድነት አለ ስንል የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው ፣ በባህላቸውና በማንነታቸው ኮርተው ሲኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

 

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች በአንዲት አገር ተከባብረው ለመኖር ብዝኃነትና አንድነትን ተቀብሎ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም ብለዋል።

 

''ብዝኃነት ኅብረብሄራዊነት ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአገሪቱ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው፣በባህላቸው፣ በታሪካቸው እንዲሁም በሃይማኖታቸው ያላቸውን ልዩነት በአግባቡና በመከባበር ማስተናገድ ካልቻልን፤አንዲት ጠንካራ አገር መፍጠር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

 

ብዝኃነት ነባራዊና ተፈጥሯዊ ሰዎች እንዲጠፋባቸውና እንዲፈርስባቸው የማይፈልጉት ማንነት በመሆኑ በአንድነት እንዲቆም ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

 

"ብዝኃነት ለኢትዮጵያ በረከት ነው ወይስ መርገም ?" የሚል በተማሪዎቹ ለቀረበው ጥያቄ ሚኒስትሩ "ብዝኃነት በአግባቡ የሚያስተናግድ ሁኔታ ከተፈጠረ ውበት ነው። ካልሆነ ግን መርገም ነው "ሲሉም ተናግረዋል።

 

ያለፉት ስርዓታት በኃይል ወደ አንድ ቋንቋ ፣ ሃይማኖትና ማንነት ለማምጣት ያደረጉት ጥረት አገሪቱን ወደ መበታተንና መፈረካከስ አዝማሚያ አድርሷት እንደነበርም አስታውሰዋል።

 

በዓለማችን ብዝኃነት በአግባቡ ማክበርና መያዝ ያልቻሉ አገሮች አንድ ቋንቋ እየተናገሩ የሃይማኖትና የፆታ እኩልነት ማክበር ተስኗቸው ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

 

የሰላም ክለብ ሱፐርቫይዘር አቶ ቴድሮስ መብራህቱ በበኩላቸው ክለቡ በዚህ ዓመት 850 አባላትን በማቀፍ በብዝኃነትና አንድነት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እንዲሁም ከተለያዩ ማህበረሰቦች ለመኖር "ዘላቂ፣ ጥልቅና አሳታፊ ውይይት ማካሄድ" የሚል ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

 

ተማሪዎቹ የተለያዩ ማህበረሰቦች በመሆናቸው "ብዝኃነትና አንድነት" ላይ ያላቸውን እውቀትና እይታ በማጎልበት ለማህበረሰቡ ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ታስቦ ውይይቱ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

 

የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዑመር መሐመድ ብዝኃነትና አንድነት ለአንዲት አገር ያለውን ጠቀሜታ ተንትነው እንዲያውቁ ማድረጉንና ይህም ለአገር ተረካቢው ትውልድ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

 

የብዝኃነት አያያዛችን ምን ይመስላል ? ብዝኃነት በስነ ዜጋ ትምህርት በማጠናከር ምን እየተሰራ ነው ? የተለየ ሃሳብ ማራመድ ተቃዋሚ ያስብላል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ለሚኒስትሩ ቀርበውላቸዋል።

 

ሚኒስትሩም ብዝኃነት የስጋትና የጥርጣሬ መንፈስ የመሆኑ ጉዳይ አብቅቶ የውበትና የምንከበርበት እንዲሁም የምንበለጸግበት ደረጃ ላይ በመድረሳችን ልንንከባከበው ይገባል ብለዋል።

 

ብዝኃነትና አንድነት በስነዜጋ ትምህርት መልክ እስከ መዋእለ ህፃናት ወርዶ እንዲያውቁት መደረግ እንዳለበትም ገልጸዋል።

 

የሃሳብ ልዩነት መኖር ለአንዲት አገር ንቃትና እድገት እንጂ፤ተቃዋሚ እንደማያሰኝ አቶ ካሳ ለተማሪዎቹ ገልጸውላቸዋል።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED