SelamAbesha.com

                

በዓለማችን በጥላቻ የተቃኘ ፖለቲካና የውጭ ጣልቃ ገብነት ብዙ ሀገራትን አፈራርሷል- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2009

በዓለማችን በጥላቻ የተቃኘ ፖለቲካ እና የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ብዙ ሀገራትን አፈራርሷል ይላሉ ምሁራን።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስ እና የመንግስታዊ አስተደዳር ምሁራን፥ መሪ አልባ ተቃውሞዎች ዜጎችን ለሞት እና እንግልት፤ ሀገራትን ለውድመት ዳርገዋል ይላሉ።

ሊቢያ፣ የመን፣ እና ሶርያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ስሜት በሚስብ ቅስቀሳ ተመርተው ወደ ተቃውሞ በመግባት የፈራረሱ ሀገራትን እንዴት መፍጠር ቻሉ በሚለው ዙሪያ ምሁራኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ሊቢያን ለዚህ ምን ዳረጋት?

በሊቢያ ዛሬ በፈራረሰ ባድማ ውስጥ የሰቆቃ ህይወትን የሚገፉት ዜጎች ከዛሬ አምስት አመት በፊት የነብስ ወክፍ ገቢያቸው 11 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ነበር።

በ40 ዓመታት የተገነባውና በአፍሪካ 5ኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የነበረው ምጣኔ ሀብቷ ግን በአምስት ዓመታት ውስጥ አፈር ድሜ በላ፤ ሊቢያውያን ከፀደዩ አብዮት ሞት እና ስደትን ብቻ አተረፉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የልማት ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ኢድሪስ የባ፥ የሊቢያን ጉዳይ እጅግ መጥፎው የፖለቲካ ቀውስ ይሉታል።

እንደ አቶ ኢድሪስ የባ፥ “የሊቢያን በሀገር ደረጃ ስናይ ትልቁ ጥፋት ነው፤ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር 2010 እና 2011 ላይ የሊቢያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአፍሪካ አንደኛ ነበር” ይላሉ።

በመካከለኛ ገቢ ከላይ ካሉ ሀገራት ውስጥ የምትመደብ ሀገርም ነበረች፤ ከዚያ በኋላ ግን በጣም በፍጥነት በተለይም ከ2012 ጀምሮ የውጭ ጣልቃ ገብነቱ መሰረታዊ ኢኮኖሚውን እየናደ መጣ ይላሉ።

ሊቢያ ውስጥ ጥያቄ ሲነሳ የወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ እና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ወዲያውኑ ጣልቃ ለመግባት የተዘጋጁት ሲሆን፥ አሜሪካንም ገፋፍተው መጨረሻ ላይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ኔቶ/ አማካኝነት ጣልቃ ገብተዋል ይላሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲው አቶ ኢድሪስ የባ።

ይህም የሆነው ሀገሪቱ ባላት ሀብት ነው፤ የዓለምን 3 ነጥብ 5 በመቶ ነዳጅ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ጣልቃ ገብነቱ በጣም ትልቅ ነበረም ብለዋል።

የዛሬይቱ ሊቢያ ግን ሰላም የራቃት፣ ጠንካታ መንግስት የሌላት፣ የታጣቂዎች መጫወቻ ሆናለች።

ሶሪያ ለምን ፈራረሰች…?

አምስት ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሶ ለሚመለከት ሰው ሶሪያ እንደዚህ አልነበረችም፤ ዜጎቿ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢን የተሻገሩ ብልፅግናንም የሚያማትሩ ነበሩ።

ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ሶርያ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይራለች።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሃዬ ምክንያቱን ይናገራሉ።

ሶሪያን ለዚህ የዳረጋት ከእነ ሩሲያ ጋር የጂዮ ፖለቲካል ፍላጎት ሊሆን ይችላል የሚለውን ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ በቀዳሚነት ያነሳሉ።

እንዲሁም ሩሲያ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ካላት ፍላጎት አንጻር፤ አሜሪካ ደግሞ በቀጥታ ከመግባት ይልቅ ከዚያው የሆኑ ፀረ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ታጣቂዎች እንዲዋጉ ማድረጓ ሀገሪቱን ለዚህ ዳርጓል የሚለውን አስተያየትም ያክላሉ።

እንዲህ አይነት በውጭ ጣልቃ ገቢዎች ፍላጎት የተቃኘ እና ግልፅ መሪ የሌለው ሁከት አዘል አመፅ ብዙ ሀገራትን አፈራርሷል።

የመን የሳዑዲ አረቢያ እና የኢራን የትግል ሜዳ ሆና ዜጎቿ እየረገፉ ሀገሪቱም እየፈራረሰች ዜጎቿ በሰቆቃ ውስጥ ናቸው።

ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ እንደናገሩት፥ በውስጥ ቀውስ በምትናጥ ሀገረ ውስጥ የውጭ ሀገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የማፈራረሱ አካል ሲሆኑ ተስተውሏል።

በዚህ መንገድ የተገባው የውጭ ጣልቃ ገብነት ሉዓላዊ እና ጠንካራ መንግስታት ያላቸውን ሀገራት ክፉኛ ያሽመደምዳል።

የውስጥ ጉዳያቸውም ከሀገራት ዜጎች ተነጥቆ በሶስተኛ ወገን የሚመራ የውጭ ሃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ ይሆናል ነው የሚሉት።

የውጭ ሀይሎች እስካልተሰማሙ ድረስ ሀገሬው እየሞተ ሀገሪቱም እየደማች ትኖራለች ብለው ሊቢያ፣ ሶሪያ እና የመንን በምሳሌነት አንስተዋል።

የመናውያን፣ ሊቢያውያን እና ሶሪያውያን ስሜት በሚስብ ቅስቀሳ ተመርተው ወደ ተቃውሞ የመጡት እንዲህ አበሳ የሚታይባቸው የፈራረሱ ሀገራትን ለመፍጠር አልነበረም።

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የዓለም ህዝብ ከዚህ ምን ይማራል…?

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ኢድሪስ፥ በዜጎች እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖር የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት የሀገርን ህልውና የሚንድ መሆን የለበትም የሚለውን በቀዳሚነት ያነሳሉ።

አቶ ኢድሪስ፥ ከሁሉ ነገር በላይ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንደ ዜጋ በራሳቸው ተነጋግረው መሄድ እና መፍታት አለባቸውም ይላሉ።

የራሱን ጉዳይ በራሱ የሚወስነው ህዝቡ ነው፤ የውጭ አካል በምንም መልኩ መግባት የለበትም፤ የውጭ አካል የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚገባው ሲሉም ይናገራሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ መረሳ ፀሃዬ በበኩላቸው፥ ዜጎች የውስጥ ግጭታቸው ለውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደሚያጋልጥ ማወቅ አለባቸው ይላሉ።

ምሁራኑ እንዳሉት የአስተሳሰብ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ እና ሊኖሩ የሚገባቸው ፀጋዎች ናቸው፤ ይህንን ማስተናገድ የሚቻለው ግን ሀገር እና ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።


Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED