SelamAbesha.com

                

ለኢትዮጵያና ሩስያ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መጠናከር ይበልጥ ሊሰራ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩስያ 120 ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያክል ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንዳለበት ተገለፀ።


በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተቋቋመው የጋራ ኮሚሽን 6ኛ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የጋራ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ተገኑ፥ “ረጅም ዓመታትን ካስቆጠረው ግንኙነት አኳያ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስራችን በደንብ ማደግ ነበረበት፤ አሁን ላይ ይህንን ለማሳደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።


የሩስያ ፌደሬሽን የተፈጥሮ ሀብት እና የአካባቢ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር እና የጋራ ኮሚሽኑ የሩስያ ሰብሳቢ ኤቭጌንይ ኬዝሌቭም፥ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሀሳብ ልዩነት የማያግደው የአለም የፖለቲካ ሞገድ የማያናውጠው ነው ይላሉ።


ግን እነዚህ ሀገራት ክፍለ ዘመን የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ላይ የሚጠበቀውን ያሀል ስኬት አላስመዘገበም ብለዋል።


አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው፥ ዛሬ በይፋ የተጀመረው 6ኛው የኢትዮጵያ እና የሩስያ መንግሰታት የጋራ ኮሚሽን ጉባኤ ዋና አለዓማ ምጣኔ ሀብታዊውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድርስ ትኩረት የሚሰጥ ነው ብለዋል።


ጉባኤው በቆይታው በሁለት ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚመክር ሲሆን፥ በንግድና ኢንቨስትመነት እንዲሁም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በባህል ትስስር ይበለጥ የሚተኮርባቸው ናቸው።


የሩስያ ፌደሬሽን የተፈጥሮ ሀብት እና የአካባቢ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ኬዝሌቭም፥ የጋራ ኮሚሽኑ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሰው መሆኑን ተናግረዋል።


ኬዝሌቭ፥ ሩስያ የኢትዮጵያ ግብርና ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲድርስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ያስታወቁ ሲሆን፥ በጋራ ኮሚሽኑ ጉባኤ ለእርሻው ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን ብለዋል።


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚና የኢትዮ ሩስያ የመንግስታት የጋራ ኮሚሽን ውስጥ የኢትዮጵያ ወገን የቴክኒክ ኮሚቴ መሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተጀመሩ ስራዎች አሉ ይላሉ።


የሁለቱ ሀገራት ገቢዎች እና ጉምርክ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች መካከል የተሳለጠ የንግድ ግንኙነት እንዲኖር የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ መሆኑንም ተናግረዋል


አቶ ጎሳዬ አያይዘውም፥ ሩስያ የኢትዮድያን የባቡር ቴከኒሽያኖችን በማሰልጠን እና ለበረካታ ዜጎች የትምህርት እድል በመስጠት የጎላ ሚና እየተጫወተች ነው ብለዋል።


ዛሬ በተጀመረው በ6ኛው የጋራ ኮሚሽን ጉባኤም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎለብቱ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም አቶ ጎሳዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ እና ሩስያ ልክ እንደ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በምጣኔ ሀብት ዘርፍም የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች ተናግርዋል።


ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 120ኛ ዓመታቸው በሚቀጥለው ዓመት ያከብራሉ።






Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED