በቀዳማዊት እመቤት ሮማን የተመራ የልዑካን ቡድን በስዊድንና በፊንላንድ የሥራ ጉብኝት አካሄደ

SelamAbesha.com

በቀዳማዊት እመቤት ሮማን የተመራ የልዑካን ቡድን በስዊድንና በፊንላንድ የሥራ ጉብኝት አካሄደ

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2009በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የተመራ የልዑካን ቡድን በስዊድንና በፊንላንድ የሥራ ጉብኝት ማካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንዳስታወቀው በቀዳማዊት እመቤት ሮማን የተመራ 20 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የሴቶች ቢዝነስ ልዑካን ቡድን በሁለቱ አገራት የሥራ ጉብኝት አካሂዷል።

የልዑካን ቡድኑ “በኢትዮጵያ ቢዝነስ እንስራ” የሚል ፕሮግራም በማዘጋጀት የኢትዮጵያን የወጪ ምርቶችና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በስቶኮልምና በሄልሲንኪ ከተሞች አስተዋውቋል።

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ጉብኝቱ የንግዱ ማኅበረሰብ ከስዊድንና ከፊንላንድ አቻው ጋር በጋራ በመስራት የሴቶችን የሥራ ፈጠራ አቅም ከማዳበር ባለፈ የገበያ ዕድሎችን የፈጠረ ነው ብለዋል።

በስዊድን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ወይንሸት ታደሰም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በሁለተኛው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ ለባለኃብቶች ገለፃ አድርገዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላትም ምርቶቻቸውን በስዊድንና በፊንላንድ ለሚገኙ ኩባንያዎች ያስተዋወቁ ሲሆን የኢትዮጵያ ምርቶችን ወደ ኖርዲክ አገራት ለማስገባት ፍላጎት ካላቸው ባለኃብቶችም ጋር ተገናኝተው መክረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቡናን በማምረት የተሰማራው ያ ኮፊ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ድርጅርትና የስዊድኑ ፊና ቦናን የተሰኘ ኩባንያ የንግድ ስምምነት መፈራረማቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED