በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያደርጉ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈረመ

SelamAbesha.com

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያደርጉ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈረመበህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጥናቶችን ከሚያደርጉ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የሶስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሁለት ጥናቶችን ከሚያከናውኑ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

 

ሶስቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በዛሬው እለት በሱዳን ካርቱም ነው።

 

ቢ አር ኤል እና አርቴሊያ የግድቡን ውሃ አያያዝ እና አለቃቀቅ እንዲሁም ግድቡን በተፋሰሱ ሀገራት ሊያደርስ የሚችለውን አካባቢያዊ እና ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን የተመለከቱ ሁለት ጥናቶችን ነው የሚያከናውኑ።

 

ጥናቶቹን ቢ አር ኤል 70 በመቶውን የሚሰራ ሲሆን፥ አርቴሊያ ደግሞ 30 በመቶውን ያከናውናል።

 

 

ሁለቱ ጥናቶች የሶስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴው በተከታታይ ባደረጋቸው ውይይቶች፣ በሚኒስትሮች ስብሰባ እና በመጋቢት ወር 2015 በግድቡ ላይ በመርህ ደረጃ በተደረሰው ስምምነት መሠረት እንደሚከናወኑም ተገልጿል።

 

የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪሲቲ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ቀጠናዊ ትብብርን ለማጎልበት ከፍተኛ ፍላጎት አላት።

 

ሀገሪቱ በሀገራቱ መካከል መተማመንን ለመፍጠር እና የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ወዳጅነትን ለማሳደግ እንደሚረዱ የሚጠበቁት ሁለት ጥናቶች እንዲከናወኑም ቁርጠኛ አቋም እንዳላት መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

 

ጥናቶቹ በሁለት ወር ውስጥ ተጀምረው በ11 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

ለአጥኚዎቹ የሚያስፈልገው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮም ከሶስቱ ሀገራት እኩል ተዋጥቶ የሚከፈል ይሆናል ።(ኤፍ.ቢ.ሲ)

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED