ማህበራዊ ሚዲያ ከጠቀሜታው ባለፈ የጎንዮሽ ጉዳት እያስከተለ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም

SelamAbesha.com

ማህበራዊ ሚዲያ ከጠቀሜታው ባለፈ የጎንዮሽ ጉዳት እያስከተለ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም

ኒው ዮርክ መስከረም 13/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ማህበራዊ ሚዲያ ለመረጃ ልውውጥ ጉልህ ጠቀሜታ ቢኖረውም አንዳንዶች የተሳሰተ መንገድ እንዲከተሉ እያደረገ ነው አሉ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ71ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ተግዳሮቶች ናቸው ያሏቸውን ችግሮች በዝርዝር አስቀምጠዋል።

 

ማህበራዊ ሚዲያ በተለይ ለመረጃ ልውውጥ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ቁርኝትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ ቢኖረውም የአሸባሪዎች መመልመያ፣ የጥላቻ መስበኪያና የተሳሳተ መልእክት እየተላለፈበት ይገኛል።

 

በተለይ ደግሞ አንዳንድ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሰተ መረጃ ወደ አልተገባ መንገድ እንዲገቡ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

 

የሰላምና መረጋጋት እጦት፣መልካአ ምድራዊ የፖለቲካ ውጥረት፣ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል እንዲሁም ሽብርተኝነት የዓለም ስጋቶች መሆናቸውንም አንስተዋል።

 

 

 

 

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦችን ለድርቅ እያጋለጠ መሆኑን ጠቁመው፤ "የዓለም ኢኮኖሚም ከገባበት ቀውስ ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቀም ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ።

 

በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠር ስደትም ቀላል የማይባሉ ችግሮችንና ሰብአዊ ቀውሶችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

በመሆኑም እነዚህንና መሰል ችግሮችን በማስወገድ ለዘላቂ ልማት እቅድ ስኬት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቡን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ በማካተት ለመተግበር እየጣረች መሆኗንም አስረድተዋል።

 

በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣችና እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና እንድትመረጥ ድጋፋቸውን ለሰጡ አገሮች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

አገሪቷ በምክር ቤቱ በሚኖራት ቆይታ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

 

ኒው ዮርክ በተካሄደው 70ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2017 እስከ 2018 የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን 185 ድምፅ በማግኘት መመረጧ ይታወሳል።

 

 

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED