መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ነው --- አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

SelamAbesha.com

መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ነው ---

አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ ነሐሴ 17/2008 በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የሁከት መንስዔ በመለየት ችግሩን ለመፍታት መንግስት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

 

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅም ሆነ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

አምባሳደር ታዬ ዛሬ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካና አውሮፓ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ጋር ተወያይተዋል።

 

ሚኒስትር ዴኤታው የችግሩን መንስዔ፣ አሁን ያለውን ሁኔታና ችግሩን ለመፍታት መንግስት እያከናወነ ያለውን ተግባር ለዲፕሎማቶቹ አስረድተዋል።

 

ከዲፕሎማቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

አሁን ለተፈጠረው ግጭትና ሁከት የመልካም አስተዳዳር ችግሮች እንዲሁም የጋራ መግባባት በሚያስፈልጋቸው የህገ-መንግስት አንቀጾች ላይ የተሟላ ግንዛቤ አለመኖር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የወጣቶች ስራ አጥነትና አገሪቷ እያስመዘገበች ባለው እድገት ምክንያት ጠያቂና ፍላጎቱ ከፍ ያለ ህዝብ በመፈጠሩ፣ ፍላጎቱን በፍጥነት በሚመልስ መልኩ መንቀሳቀስ አለመቻልም ሌሎች ምክንያቶች ናቸው።

 

በአገሪቱ ለተፈጠሩት አለመግባባቶችና ግጭቶች ምክንያታዊ የሆኑና ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች መኖራቸውን ያመለከቱት አምባሳደር ታዬ፤ አሳማኝ ያልሆኑና ሌላ ፍላጎት ያነገቡ ጥያቄዎችም መንጸባረቃቸውን ተናግረዋል።

 

ሆኖም መንግስት መልስ ለሚያሻቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና የህዝብ ቅሬታዎችን ከመሰረቱ ለመፍታት ከህዝብ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል።

 

በአሁኑ ወቅት ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፉ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

 

ግጭቱ ተከስቶ የነበረባቸው አካባቢዎችም በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

 

በመድረኩ የተገኙ ድፕሎማቶች በበኩላቸው መንግስት ችግሩን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ከተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሲቪል ማህበራት ጋር አብሮ መስራት እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

እንደ ዋና ጉዳይ የተለየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት እየተወሰዱ ባሉ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲሁም በህገ መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይም ማብራሪያ ጠይቀዋል።

 

የደረሰውን የጉዳት መጠንና ህይወቱ ያለፈውን ሰው ቁጥር ብዛት የተመለከቱ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።

 

አምባሳደር ታዬ በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት የተፈጠረውን ችግር መንስዔውን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነትና ይህን የሚያደርግ ስርዓትም መኖሩን ገልጸዋል።

 

የደረሰውን የሞትና የንብረት ውድመት በተመለከተ ትክከለኛውን ቁጥር ለማወቅም ሆነ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሸን የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED