ህወሓት በድርጅቱ ላይ እያንዣበቡ ያሉትን ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት መወሰኑን አስታወቀ

SelamAbesha.com

ህወሓት በድርጅቱ ላይ እያንዣበቡ ያሉትን ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት መወሰኑን አስታወቀ

መስከረም 15፣ 2009

መስከረም 15፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ከመስከረም 9 እሰከ 13 2009 ዓ.ም ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አጠናቋል።

 

ኮሚቴው የህዳሴ ጉዞ ድሎችና በድርጅቱ የታዩት አደጋዎች፣ ተግዳሮቶችና ምንጫቸው፣ ፖለቲካዊ ትርጓሚያቸው እንዲሁም መፍትሄያቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው በጥልቀት ገምግሞ ስብሰባውን ያጠናቀቀቅ።

 

 

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ባለፉት 15 የተሃድሶ አመታት ያስመዘገባቸው ድሎች በገመገመበት ወቅት የትግራይ ህዝብ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተሰባስቦ በገጠርና ከተማ በልማት፣ በዴሞክራሲና ሰላም አንፀባራቂ ድሎች በማስመዘገብ የተሃድሶ መሰመሩን ህያው ማድረጉን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አረጋግጧል፡፡

 

የትግራይ ገጠር ነዋሪው ህዝብ ኑሮውን ለመቀየር በመሪው ድርጅት ህወሓት የተቀየሰውን ግብርና መር ስትራቴጂ ለመተግበር በተደራጀ የልማት ሰራዊት ባደረገው እንቅስቃሴና ትግል አመርቂ ድሎች ማስመዝገቡ መቻሉንም አመላክቷል።

 

 

የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ በጦርነትና ድርቅ የተጋለጠውን የትግራይ ክልል በአረንጋዴ ልማት ለመለወጥ የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች ተአምራዊ ውጤት ለግብርናና የገጠር ልማት ስራዎች መሰረት የጣለ መልካም ተሞክሮ መሆኑን አረጋግጠናል ብሏል።

 

ይህንን ስራ የመስኖ አቅም እንዲጎለብትና በድርቅ የማይበገር የግብርና ኢኮኖሚ እየተገነባ እንዲሄድ የላቀ አስተዋፅኦ ተጫውቷል ነው ያለው።

የተሃድሶ መስመሩ በገጠር ብቻ ሳይወሰን በጥቃቅና አነስተኛ ስትራቴጂ የከተማ ህዝብ ኑሮ ለመቀየር ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ ማስመዘገብ መጀመሩ መግለጫው አመላክቷል፡፡ በዘርፉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቁሟል።

በማህበራዊ ልማት በትምህርትና ጤና ዘርፍም የእድገቱ መሰረት ለመጣል የሚያስችል ስራ መሰራቱ አረጋገጣናል ብሏል።

 

ምንም እንኳ በልማታዊና ዴሞክራሰያዊ መስመሩና በህዝቡ ተሳትፎ እነዚህ ድሎች ቢመዘገቡም የተጀመረውን ለውጥ ወደኃላ የሚመልሱ፣ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የአመራር ጉድለት እንዳሉ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በጥልቀት ገምግሟል፡፡

የችግሮቹ መነሻ ያላቸው እስካሁን የተመዘገበው ድል የፈጠራቸው ተጨማሪ ፍላጎቶች በአግባቡ መልስ ባለመሰጠቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተሃድሶው ወቅት የተለዩ የስርአቱ አደጋዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በፅናት በመመከት ከምንጩ እየደረቁ ባለመሄዳቸው መሆናቸውን አመላክቷል።

 

ለፍትህ ብሎ ሁሉም አይነት መስዋዕት የከፈለ ህዝብ መልካም አስተዳደር ልናሰፍንለት አልቻለንም ያለው ኮሚቴው፥ ይህም የስርአቱ ተረካቢ ወጣቱ ትውልድ በራሱ የተደራጀ ተሳትፎ ተጠቃሚነቱ ለማረጋገጥ ብሎም ለአጠቃላይ ግንባታው የተደረገው ትግልና እንቅስቃሴ ደካማ እንደነበር ገምግሟል።

የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድም ጉደለት መኖሩንና በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና በድርጅቱና ህዝቡ ፍላጎት አኳያ የሚጠበቅ ደረጃ አለመሆኑን መረጋገጡ ኮሚቴው አስታውቋል።

 

ስልጣንን ለህዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከማዋል ይልቅ ለግል ጥቅምና ክብር መጠበቂያ አድርጎ መወስድ የሁሉም ችግሮች ምንጭ መሆናቸው ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

 

በድርጅቱ በየጊዜው ቦታ እያገኘ የመጣው የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የአድርባይነት ችግሮች በድርጅቱ የነበረውን መደባዊ ትግል እንዲደበዘዝ ምክንያት ሆኗል ብሏል መግለጫው።

በአጠቃላይ እንደ ድርጅት እና ህዝብ የማይገልፁት ቢሆንም የጠባብነት ምልክቶች እንዳሉ መገምገሙንም አመላክቷል።

 

በተለይ የጎጠኝነት አስተሳሰብ ጎልቶ የሚታይ ችግር መሆኑንና ቀጣይ ትግል ካልተደረገበት የሚፈታተን አደጋ መሆኑ እንደማይቀር አፅንኦት ተሰጥቶታል።

ማእከላዊ ኮሚቴው በውስጥ ችግርና በህዝቡ የተፈጠረው ያለመርካት እንደ መልካም እድል በመጠቀም በድርጅቱና በህዝቡ መካከል ክፍተት በመፍጠር የህዳሴውን ጉዞ ለማደናቀፍና ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ፀረ ህዝብና ሰላም ሃይሎች እየፈጠሩት ያሉትን አደጋዎችና አፈታት ዙርያም በጥልቀት ገምግሟል።

 

በድርጅቱ እያንዣበቡ ያሉትን ችግሮችም የአጭርና የረዥም የትግል ስልቶችን በአፋጣኝ በመቀየስ ለመፍታት ውሳኔ ላይ መደረሱን ነው ያስታወቀው።

 

በአጭር ጊዜ ቀጣይና ሰፊ ትግልና የማጥራት ስራ ለማካሄድ፣ የተጠያቂነት መርህ መሰረት በማድረግ ሽግሽግና ማስተካካያ በማድረግ ማዕበላዊ እንቅስቃሴ ለመለኮስ መወሰኑን በመግለፅ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርቧል።

 

 

 

 

 

 

Selamabesha.com

Hosted By Fissha Belay

© COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED